Sunday, June 24, 2012

በአዋሳ ከተማ ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ነው


ሰኔ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአዋሳ ከተማን እጣ ፋንታ እና የሲዳማ ዞንን የክልል ጥያቄ ተከትሎ በሲዳማ ዞን ተወላጅ የምክር ቤት አባላት በአንድ ጎን እና የፌደራሉና የሌሎች የምክር ቤት አባላት በሌላ ጎን ሆነው  የጀመሩት ውዝግብ እየተካረረ መምጣቱን ተከትሎ በአዋሳ የሚታየው ከፍተኛ ውጥረት አለመቀነሱን ዘጋቢያችን ገልጧል።

በዛሬው እለት ወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ በሚል ስጋት የፌደራል ልዩ ሀይል አድማ በታኝ ፖሊሶች በከተማዋ በጂፕ መኪኖች ላይ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ቅኝት ሲካሂዱ ውለዋል። ዛሬ ምንም አይነት ግጭት አለመከሰቱን የገለጠው ዘጋቢአችን ይሁን እንጅ ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በማንኛውም ሰአት ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በማለት ስጋቱን ገልጧል። ወረቀቶች መበተናቸውን መቀጠላቸውን፣ ሌሊቱን የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር፣ በከተማዋ ዳርቻ የሚገኙ ሱቆች አሁንም ዝርፊያ በመፍራት መዘጋታቸውን ገልጧል።
ጉዳዩን በማስመልከት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የደቡብ ተወካይ የሆኑትን አቶ ዳንኤል ሽበሽ ለኢሳት እንደተናገሩት፣ በአዋሳ የተነሳው ግጭት ከመልካም አስተዳዳርና ፍትህ እጦት ጋር የተቆራኘ ነው።
በ1994 ዓም በተፈጠረው ችግር በርካታ ዜጎች ማለቃቸውን ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፣ የአሁኑ ችግር ከ10 አመት በሁዋላ አገርሽቶ የመጣው መንግስት ችግሩን በወቅቱ ለመመለስ ባለመቻሉ ነው
አሁን በአካባቢው የሚታየው ውጥረት ወደ ብሄረሰብ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉ፣ እርስዎ እንዴት ያዩታል ለተባሉት አቶ ዳንኤል ስጋቶች መኖራቸውን ተናግረዋል::

No comments:

Post a Comment