Friday, November 18, 2011

ግንቦት 7 እና የኢትዮጵያ አንድነት !

ብርሃኑ ነ.


መግቢያ 
በመጀመሪያ ይህን ስብሰባ ያዘጋጀው የኢትዮጵያውያን ህዝባዊ ፎረም ድርጅታችንን ግንቦት 7ትንና
ድርጅታችን አባል የሆነበትን ጥምረት ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነትን (ጥምረት)  ወክዬ በዚህ ስብሰባ
እንድገኝ ስለጋበዘኝና፤ በዚህ ስብሰባ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆናችሁ እዚህ ለተገኛችሁ ወገኖቼ የከበረ
ምስጋናየንና ስላምታየን አቀርባለሁ::
በእንዲህ አይነቱ ስብሰባ በተገናኘን ቁጥር እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ ትንሽም ቢሆን የረባ ስራ ሰርተንበት
መሄድ ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ። ጊዚያችን፣ ጉልበታችን፣ ገንዘባችንና   ስሜታችንን ፈሰስ አድርገን
እንዲህ አይነቱን ስብሰባ ስናዘጋጅ አላማው ትንሽም ቢሆን የፓለቲካ ሰዎች ነን፤ የሁሉንም የሃገሪቱ ህዝብ
ወይም በተወሰነ ክልል ያለው ህዝብ ስቃይና መከራ ከምር ያሳስበናል በምንል ሃይሎች መሃል የጋራ
መግባባት ለመፍጠሪያነት እና ትንሽም ቢሆን በመሃከላችን ያለውን ያለመግባባትና ብዥታ ለማጥሪያና
በሁላችንም ላይ ከተከመሩብን ተራራ የሚያካክሉ ብሄራዊ ችግሮች የተወሰነውን ለማቃለል ትንሽ እገዛ
የሚያደርግ ስብሰባ ሊሆን ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ።
ከዚህ እምነት በመነሳት ለእንዲህ አይነቱ ስብሰባ ስጋበዝ ጊዜ ወስጄ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት
አስብበታለሁ። በእንዲህ አይነቱ ስብሰባ የምናደረገው ንግግር የምንገጥመው ሙግትና ክርክር
የምንጠመድበት ውይይት በዚህ አዳራሽ ውስጥ ታጥሮ የሚቀር ሳይሆን ከዚህ ስብሰባ አዳራሽ ውጭ
ወደሚገኙ በሽዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ጆሮ የሚደርስ፣ በጎም ክፉም መዘዞች ያሉት
እንደሚሆን ስለማውቅ በሚገባ መዘጋጀቱን እመርጣለሁ። ለዚህም ነው፥ በበርካታ ስብሰባዎች ላይ
የማደርገውን ንግግር በጽሁፍ ማቅረብ የምመርጠው። በጽሁፍ ማቅረቡ ሌላም ጠቀሜታ አለው። ይህ
ስብሰባ ካለቀ በኋላ በስበሰባው ያልተገኙ ወይም ስብሰባውን በሌሎች ሚድያዎች ለመከታተል ያልቻሉ
ወገኖቻችን በዚህ ስብሰባ እኔም ሆንኩ የግንቦት7 ንቅናቄ የሚያቀርባቸውን ሃሳቦች በስማ በለው ሳይሆን
በቀጥታ ማንበብ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠሩ፤ ጠባብ ለሆነ ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም ሲሉ ከንግግሮቻችን
መሃል ነገሮችን ከማእቀፋቸው እያወጡ ወይም ያልተባለውን ተብሏል በማለት በማህበረሰባችን ውስጥ
ውዥንብርና  ሁካታ ለመፍጠር ቆርጠው የተነሱ አካላትን መሄጃ የሚያሳጣ ይሆናል::
በጽሁፍ የማቀረበው የዛሬው መልዕክቴ ዋናው ትኩረቱ ከሃገር፣ ከዜጎች እና ከህዝቦች አንድነት ጋር
በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ይሆናል። በዚህ ርእስ ስር የማነሳቸው ጉዳዮች በዋንኛነት የግንቦት 7 የፍትህ፣
የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በአንድነት ጥያቄ  ላይ ያለውን ግንዛቤና አቋም ምን እንደሆነና ለምን ይህን
ግንዛቤና አቋም እንደያዘ ለማሳየት ነው። ይህን ርዕስ የመረጥኩት ይህ ጉዳይ በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ
ትናንትም ዛሬ መሰረታዊ ጥያቄ በመሆኑ ነው። ዛሬም እንደትናንቱ በአንድነት ጉዳይ ላይ በህብረተሰባችን
ውስጥ ያለው አመለካካት ከውንዥንብር የጠራ አይደለም። ይህ ውዥንብር የሃገራችን ህዝብ፣ በወያኔ
የተጫነበትን ዘረኛ የሀገር ውስጥ የአፓርታይድ አምባገነናዊና ዘራፊ ስርአት በጋራ ትግል አስወግዶ
በአንድነት መብቱን አስከብሮ  ሰላም አግኝቶ  እያዋረደው ካለው ድህነት ራሱን አላቆ በአለም ህብረተሰብ
ፊት አንገቱን ቀና አድርጎ   እንደሰው የሚታይበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እያደረገ የሚገኝ ታላቅ እንቅፋት
ነው የሚል እምነት አለኝ። የማደርገው ንግግር ትንሽም ቢሆን ይህን ውዥንብር በማጥራት ብዙዎቻችን
በአንድነት ጉዳይ ላይ አይን ለአይን እንድንተያይ ለማድረግ ያግዛል ብዪ አምናለሁ። ለግልጽነትና  በዚህ
ስብሰባ ውስጥ ለምናደርገው ውይይት እንዲረዳ ንግግሬ በተለያዩ ሶስት ንዑስ ርዕሶች ከፋፍዬ
አቀርባለሁ።
የመጀመሪያው ንኡስ ርእስ የአንድነት ጉዳይና የግንቦት 7 ንቅናቄ የሚል ይሆናል። በዚህ ርእስ የግንቦት 7
ንቅናቄ  በድርጅታዊ ፕሮግራሙና በንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብ (bylaw) ውስጥ አንድነትን በሚመለከት
ያሰፈረውን የንቅናቄውን እይታና አቋም በአጭሩ አቀርባለሁ። ይህን በማድረግ የግንቦት 7  ንቅናቄ
በአንድነት ጉዳይ ላይ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚያንጸባርቃቸውን አቋሞችም ይሁን በተጨባጭ
የሚፈጽማቸውን ድርጊቶች ከምን እንደሚመነጩ ምክንያታቶቹም ምን እንደሚሆኑ ለሁሉም ግልጽ
ማድረግ ይቻላል ብዬ አምናለሁ።
በሁለተኛው ንኡስ ክፍል  የማተኩረው በአንድነት ጥያቄ ዙሪያ የሚነሱ፣ ግን ዛሬ ያለንበትን የወል ወይም
የጋራ አዋራጅ ሁኔታ በመቀየር ብሎም የወደፊቱን ትውልድ ከውርደት ውርስ ለማዳን ምንም ፋይዳ
የማይኖራቸውን ጉዳዮች በማንሳት በአንድነት ጥያቄ   ውይይታችን ፊት እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ
የማስባቸው ጉዳዮች ላይ ይሆናል። በዚህ ክፍል የማቀረበው ገለጻ በጽሁፍ የቀረበ ታሪክን ሃቅንና
እውነትን፣ የሚያጣቅስ ቢሆንም አቀራረቤ አየር ላይ የተንሳፈፈ አብስትራክት ወይም አካዳሚያዊ እሰጣ
አገባ አይሆንም። ሁላችንም በጋራ ለገባንበት ተጨባጭ ችግር ተጨባጭ መፍትሄ ሊሰጥ በሚችል እይታ
የማቀረበው ይሆናል። ይህ ክፍል ቀደምቶቻችን ዘመናዊ ሃገርና መንግስት ለመገንባት ባደረጉት ጥረት
የገጠሟቸውን ድልና ፈተናዎች የምፈትሽበት እንዴትም ከዘመናዊ ሃገርና መንግስት ምስረታ ድሎች
የበለጠ ፈተናዎቹ የበዙ ሆነው ለትውልድ መተላለፍ እንደቻሉ የማሳይበት ይሆናል። ከዚህ ፈተና3
ለመውጣት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማናችንም የፍጹም ሃቆች ወይም እውነት (absolute truth) ጌቶች
መሆን እንደማንችል በተለይ የታሪክና   የማህበራዊ ሃቆችና እውነቶች እንደ ሂሳብና ሳይንስ እውቀቶች
ሁላችንም የግድ መቀበል የሚገባን ሳይሆኑ በውይይት በድርድርና ስምምነት የምንደርስባቸው
እውነቶች/ሃቆች (negotiated truth) እንደሆኑ በተጨባጭ ምሳሌዎች ለማሳየት የምሞክርበት ይሆናል።
ይህን አለመረዳት በማያስፈልግና ችግራችንን ለመፍታት በማያስችል አቅጣጫ ብዙ የግዜና ጉልበት
ግብአት እንዳባከንን የሚጠቁም ይሆናል። በዚህ አቀራረብ አምክህኖን (reason/rational)  ከፖለቲካ
እያራቅን በስሜት ብቻ የምንነዳበት ሁኔታ ውስጥ ስንወድቅ፣ እንዴት መደማመጥ እንደሚጠፋ፣ እንዴት
ሊያቀራርቡን ከሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ይበልጥ የሚያለያዩን ጉዳዮች እየሰፉ የሚመጡ መሆኑን ለማሳየት
ጥረት የማደርግበት ይሆናል። አቀራረቤ ሊያስማሙን የሚችሉ ብዬ  የማስባቸውን ከአንድነት ጉዳይ ጋር
የተያያዙ መሰረታዊ ጉዳዮች ግልጽና   በማያሻማ ቋንቋ   በመሰንዘር እያንዳንዳችን በቀና   መንፈስ
እንድናሰላስላቸው መጋበዝ ይሆናል።


To read all the document pleas click the following link ,

No comments:

Post a Comment